ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚረዳ ፖሊሲ ሥራ ላይ መዋሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚረዳ ፖሊሲ ሥራ ላይ መዋሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስተኛውን የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ስለ ሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዚህም የሳይበር ጥቃት በአገራት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት፣ ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎችና መፍትሄዎች ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርአያ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤የሳይበር ስጋት እየጨመረ ቢመጣም ተያያዥ ችግሮችን በመከላከል ከዘርፉ ለመጠቀም መስራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

የሳይበር ጥቃት ከጊዜው ጋር እየዘመነ መሆኑን ጠቁመው፦ አሁን ያለውን አውድ የሚመጥን አሰራር መዘርጋት ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ተሻሽሎ የወጣው የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉን ገልጸው ፖሊሲው ከሳይበር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት ያለመ ነው ብለዋል።

ዜጎች ስለ ሳይበር ደህንነት በቂ ግንዛቤ አለመያዛቸው፣የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል እጥረቶች ፈተና መሆናቸውን ጠቁመው ፖሊሲው በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን መያዙን አብራርተዋል።

ዜጎች በሳይበር ደህንነት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ፣ በመስኩ ጥናትና ምርምሮችን በሰፊው ማካሄድና አገራዊ የመከላከል አቅምን ማሳደግም የፖሊሲው ግቦች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ ግንዛቤን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻውን መቀላቀሉ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው የሳይበር ጥቃት በተለይም በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጥረው ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ለአብነት አንስተዋል።

በባንኩ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ባንኩ በዘረጋው አሰራር መመከት መቻሉን ገልጸው፥ይሄው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በርካታ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(አይ ቲ) መመሪያዎችን ሥራ ላይ ከማዋል ጀምሮ የሰራተኛውን አቅም የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማረ አሰፋ እንደገለጹት፤ባንኩ ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመከላከል በቴክኖሎጂ ራሱን የማስታጠቅ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ 80 በመቶ በላይ የባንኩ ግብይት የሚፈጸመው በዲጂታል መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለዚህ የሚረዳ አስተማማኝ የደህንነት ሥርዓት መዘርጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

ለዚህም ባንኩ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ ከመቀመር ጀምሮ ዘመኑ የደረሰበትን አሰራር በመከተል ውጤታማ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም ለ21ኛ ጊዜ በኢትየጵያ ደግሞ ለ 5ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም