ቀጥታ፡

ሰላምን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡ ተሳትፎ የላቀ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ 

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ሰላምን አጠናክሮ በማስቀጠል ሂደት የህዝቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የፌዴራልና የክልል የሰላምና ጸጥታ ተቋማት የተሳተፉበት የሰላም ኮንፍረንስ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ እንደገለጹት ሰላምን በጸጥታ ኃይል ጥረት ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም።

በክልሉ ሰላምን ለማጽናትና አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው በዚህ ረገድ ለተገኘው መልካም ውጤት የህዝቡ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ ሰላምን አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ህዝቡ ተደራጅቶና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ አመልከተዋል።

የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች  እንዲያብቡ በማድረግ ሰላማችንን አጠናክረን ማስቀጠል ችለናል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።

በክልሉ ባለሀብቶችን ጨምሮ ህዝቡ በተለይም የፖሊስ ተቋማትን የማጠናከር ተግባር በመደገፍ ለሰላም መረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በሎጂስቲክስና በቁሳቁስ ይበልጥ በማጠናከር ከህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ተልእኮ በሚገባ እንዲወጣ ይሰራል ብለዋል።


 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ በበኩላቸው፤ አብሮነትና መቻቻል የሰላም መሠረት በመሆናቸው ይህንን ለማጽናት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ሲዳማ ክልል በ"አፊኔ" ስርዓትና የሰላም አደረጃጀት በመጠቀም  አበረታች ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

ክልሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በህዝቡና አመራሩ ጥንካሬና ቁርጠኝነት ሌሎች ክልሎች ልምድ ሊሆን የሚችል የሰላምና ደህንነት ስራ ማከናወኑን አድንቀዋል።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው "ጠንካራ የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋትና ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በተሰራው ስራ ሰላሙ የተጠበቀ ክልል መገንባት ችለናል" ብለዋል።


 

በክልሉ የሰላም ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ ሆኖ እየተመራ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው በክልሉ የዳበረ ሰላም  እንዲሰፍን  የላቀ አስተዋጾ ላበረከቱ 298  አመራርና  የፖሊስ አባላት እስከ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር የማዕረግ  እና የደረጃ እድገት መሰጠቱን አስታውቀዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም