ቀጥታ፡

የሀዋሳ የኮሪደር ልማት ስራ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚሰጥና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ):- በሀዋሳ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚሰጥና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎችና አመራር አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ላይ የተሳተፉ ከ100 በላይ የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎችና አመራር አባላት የሃዋሳ ከተማን የኮሪደር ልማት ስራ ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረር ከተማ፣ የሽሬ እንደስላሴ ከተማ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችና አመራር አባላት የሃዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚሰጥና ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንደሚሆን ነው የገለጹት።

የሐረር ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ዮኒስ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የከተሞችን ውበት፣ ጽዳትና ገጽታ የሚቀይረው የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ያለበት ወቅት ነው።

በሃዋሳ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪው ምቹ እንደሚያደርጋት ጠቅሰው፤ ስራው የሚከናወንበት መንገድ ለከተማችን ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

የሃረር ከተማም ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት መግባቷን አስታውሰዋል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ ባዳሬ በበኩላቸው፤ በሀዋሳ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ተጨማሪ ውበት ከመሆን ባሻገር ሰፋፊ መንገዶችና የአረንጓዴ ልማት ስራዎቿ ለነዋሪዎች ምቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከከተማው የወሰዱትን ልምድ ወደ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመቀየር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሽሬ እንደስላሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብረመድህን ዮሃንስ፤ የሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማትና መሰረተ ልማት እንቅስቃሴ ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በከተማው የኮሪደር ልማት ስራ ላይ ህብረተሰቡ በባለቤትነት መሳተፉን እንደመልካም ተሞክሮ ገልጸው፤ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የተጀመረው የህብረተሰብ ተሳትፎ ስራ ውጤታማ ነው ብለዋል።

ከሀዋሳ ያገኙትን ተሞክሮ በመቀመር በአካባቢያቸው ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በከተማው በሶስት ምዕራፍ የተከፈለ የኮሪደር ልማት የተጀመረ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዙር ስድስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ የሚሸፍን ነው።

ከዚህ ውስጥ የአንድ ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ስራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ቀሪው የወሰን ማስከበር ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ለኮሪደር ልማቱ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ የገለጹት ከንቲባው፤ ህብረተሰቡ ይዞታውን በማንሳት ለልማቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ 101 ከተሞችን በአባልነት ያቀፈና ከተሞች እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ የከተሞችን መሰረተ ልማት በማሳለጥና የአመራሩን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም