ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያከናውናቸው የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት መሠራት አለበት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራዝ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ የሚያከናውናቸው የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እንዲሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዩኒቨርሲቲውን የ2017 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የዩኒቨርሲቲውን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) አቅርበዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መቋቋሙ ይታወሳል።

ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) በሪፖርታቸውም፤ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ራስ ገዝ ሆኖ መቋቋሙን ተከትሎ ተቋሙን በአዲስ መልክ የማደራጀትና መመሪያዎችን፣ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አመላክተዋል።


 

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም ተቋሙን መልሶ የማዋቀርና ተማሪዎችን ተቀብሎ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የተማሪዎች የቅበላ ፖሊሲ፣ የሰው ኃብት ልማት መመሪያና የጥቅማጥቅም ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንዲሁም የውስጥ ገቢ ማሳደጊያ ሥልቶች ተነድፈው ተግባራዊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የቅበላ ፖሊሲው ጥራት ከግምት ባስገባ መልኩ ፍትኃዊነትን፣ አካታችነትንና ስብጥር ባረጋገጠ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል።

እንዲያም ሆኖ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ አልፎ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ጉድለቶችን ለማረም በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነት ሽግግር የሚመራበትን ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀቱና የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች እንዲሻሻሉ ማድረጉ በጥንካሬ የሚነሳ ነው ብለዋል።


 

የኒቨርሲቲው የራሱን የቅበላና የክፍያ ፖሊሲ ማዘጋጀቱና የውስጥ ገቢ ማሳደጊያ ሥልቶችን መቀየሱ ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው ጠንካራ ጎን መሆኑን አንስተዋል።

ነገር ግን ከተማሪዎች ቅበላ ስብጥር አኳያ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ቅበላ ክልሎችን፣ ፆታ፣ አካል ጉዳተኞችን ስብጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መፈጸም እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነት ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ሪፎርም መሥራትና በየዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል መመደብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለመምህራንና ለተመራማሪዎች ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር አኳያም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ምንጭ የመሆን፣ አገርን የማሻገርና ምሁራን የሚፈልቁበት ተቋም የመሆን አደራውን እንዲወጣም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም