ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማጽናት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ፡፡

28ኛው የኢትዮጵያና ጂቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳደሮችና ኮሚሽነሮች ስብሰባ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።

ስብሰባው በሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የጋራ ልማት ላይ ይመክራል። 

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትከተላለች።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በኢጋድ ቀጣና የሚገኙና በህዝብ ለህዝብ፣ በኃይል አቅርቦት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር  ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የድንበር አስተዳደሮችና ኮሚሽነሮች የጋራ ስብሰባ በድንበር አካባቢ ትብብር ከመፍጠር ባለፈ የጋራ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መምከር የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በድንበር አካባቢ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማስቀጠል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አንስተዋል።

ስብሰባው አገራቱ ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም፣ ቀጣይነት ያለው ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን እንዲሁም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።

ለኢኮኖሚ እድገትና ዘላቂ ሰላም እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ትብብርና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ በተጨማሪ ከሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር ሽብርተኝነትን፣ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እና የእንስሳት እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የጂቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ሱሌይማን ሙአሚን በበኩላቸው፤ 28ኛው የኢትዮጵያና ጂቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳደሮችና ኮሚሽነሮች ስብሰባ የሁለቱን አገራት ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት ለማፅናት የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

የጋራ ስብሰባው ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ የድንበር ግንኙነቱን ማሳለጥ፣ በድንበር አካባቢ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል የሚመከርበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ የሚገኙበት ቀጣና በተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተሞላ መሆኑን ገልጸው፤ ሁለቱ አገራት ይሄንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትብብራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የዚህ ኮሚቴ ተልዕኮም የድንበር አካባቢዎችን ሰላም ማስከበር መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ ጂቡቲ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል።


 

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሀኑ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ጂቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳደሮችና ኮሚሽነሮች ስብሰባ የሀገራቱን ትብብር ዘላቂ ለማድረግ የሚዘጋጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ እቃዎች በብዛት በጅቡቲ በኩል እንደሚመጡ ገልጸው፤ በድንበር አካባቢ ያለውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር በኩል የሚታዩ ችግሮች ቢኖሩም በትብብር በመስራታችን መሻሻሎች ታይተዋል፤ ይሄም ተጠናክሮ ይቀጥላል  ነው ያሉት፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም