ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና በህዝቦች መካከል የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር እንሰራለን -የአለም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና በህዝቦች መካከል የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር እንሰራለን -የአለም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና በህዝቦች መካከል የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እንዲዳብር እንደሚሰሩ የአለም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለፁ።
የሰላም ሚኒስቴር በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢንዛይድ ፎር ሂዩማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው የአለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተጠናቋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድነት ፓርክ ጉብኝት አድርገዋል።
በተመለከቱት ነገር መደነቃቸውን በመግለጽ በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ለውጦች የሚደነቁና ተጠናክረው መቀጥል የሚገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በአለም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ የአብሮነትና የመቻቻል ባህሎች እንዲዳብሩ እንሰራለን ብለዋል።
በደቡብ ሱዳን የሃይማኖት ተቋማት ዋና ፀሃፊ ፔርተር ያይድንግ ከጉባዔው የህዝቦችን የመቻቻልና ተከባብሮ የመኖር እሴት ለማዳበር የሚያስችል ትምህርት እንዳገኙ ተናግረዋል።
የአፍሪካም ይሁን የአለም ህዝቦች በመቻቻልና በመተባበር ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ለልማትና ለእድገት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውን ለሰላም ተባብረው መስራታቸውን ተከትሎ ከተሞች በፈጣን እድገት በመታገዝ የሚያስደንቅ ገፅታ እየተላበሱ መምጣታቸውን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ከደቡብ አፍሪካ የሃይማኖቶች ምክር ቤት የመጡት ራቢ ግላድ ፍሪድማን ጉባዔው የአለም ህዝብ በመቻቻል አብሮ እንዲኖር ለማስቻል የሚረዱና ትምህርት ለመስጠት የሚያስችሉ ልምዶችን የተጋሩበት እንደነበር ተናግረዋል።
በአለም ላይ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን በርካታ ግጭቶች መከሰታቸውን በመጥቀስ ግጭቶች እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው በሃይማኖት አባቶችና መሪዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ፈጥርን ባለመስራታችን ነው ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችን ግንኙነት በማጠናከር መቻቻልና ሰላም እንዲሰፍን ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጉባኤው የአለምን አንድነትና ተመሳሳይነት በመገንዘብ ህዝቦች አብረው እንዲኖሩና እንዲሰሩ የሚያስችል ስራ ለመስራት ትልቅ እድል መፍጠሩን በኡጋንዳ የሙስሊም ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ ሙሀመድ አሊ አሉማ ተናግረዋል።
ሁላችንም የሀይማኖት፣የቀለምና የባህል ልዩነት ቢኖረንም አንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን ብለዋል።
ልዩነቶችን በማክበር፣ በመቻቻልና አብሮ በመኖር በጋራ በመልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአለም የሃይማኖት ጉባኤን በሚያስደንቅ መልኩ በማዘጋጀቱ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።