ቀጥታ፡

ከረሀብ ነጻ አለምን ለመፍጠር የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ከረሀብ ነጻ አለምን ለመፍጠር የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የኬንያና የሴራሊዮን ሪፐብሊክ መሪዎች ገለጹ።

"ከረሀብ ነጻ ዓለም" ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሶስተኛ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሌስ ማዳ ባዮ፣የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪባ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ ሼክ ሻክቦት ቢን አልናህያን በተገኙበት በአድዋ መታሰቢያ ተካሂዷል።


 

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በዚሁ ጊዜ፤የእኩልነት መጓደል፣ የተንሰራፋ ድኅነት፣ግጭትና የአየር ንብረት መዛባትና ረሃብ መፍትሄ የሚሹ አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተለይም በግጭትና የተፈጥሮ አደጋ እየታመሰች ላለችው ዓለም ረሃብን ማጥፋት አፋጣኝ ምላሽ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

ከዚህ አሳዛኝ ውድቀት የምንወጣበት ብቸኛ መንገድ የጋራ ትብብር ሲኖር ነው ብለዋል።

በመሆኑም ረሃብን ለማዋጋት ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት ዊሊያም ሩቶ።

ይህም ብቻ ሳይሆን እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ለመመገብ የምግብ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም የግብርናና የምግብ ሥርዓት እምቅ አቅምን ከፍ ለማድረግ ጊዜው አሁን መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘላቂነት ያለው ምርት በሁሉም የእሴት ሰንሰለቶች ውስጥ የምግብ ሥርዓቶቻችንን ማስፋፋትና ጠንካራ የምግብ ሥርዓቶችን መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የታለሙ ስልቶችን ቅድሚያ በመስጠት የግብርና ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አየር ንብረትን በመቋቋምና በምግብ ዋስትና መካከል ያለውን አዎንታዊ ትስስር በመጠቀም በቂ ኃብቶችን ማሰባሰብና ማሰማራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው "ከረሃብ ነፃ ዓለም" ጉባዔ የጋራ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዕድል የፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታትና አቅምን ለማጎልበት ለሚያደርጉት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል።


 

የሴራሊዮን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ በበኩላቸው እንዳሉት በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በምግብ ዋስትናና በተመጣጣነ ምግብ እጦትና በረሃብ ላይ ይገኛል።

የምግብ ዋስትና እጦት በሁሉም የሕይወት ገጽታ ላይ ተጽእኖ እንደሚያደርስ ጠቁመዋል።

ችግሩ በልጆች እድገት፣በትምህርት ስኬታማነትና በወደፊት የህይወት እድሎቻቸው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አመላክተዋል።

እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፋዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምግብ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑንም አንስተዋል።

የምግብ ዋስትና እጦት እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት አህጉራት ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ምሁራን ፣ ሲቪል ማህበረሰቡ እና የግሉ ሴክተር፣በአፍሪካ እና በአጠቃላይ የአለም የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነት የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አስተዋጽኦ ስላላቸው ለውጥ ለማምጣት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የወሰደቻቸው እርምጃዎች በምሳሌነት የሚነሱ መሆናቸውን በመጥቀስ ከረሀብ ነጻ አለምን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ሊሳካ እንደሚችል ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋማትን ማጠናከር እና ደጋፊ የፖሊሲ ምህዳርን መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም