ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የስራ ፈጠራ ክህሎትን የማጎልበት ተግባር በትኩረት እየተከናወነ ነው

መቀሌ፤ ጥቅምት 28/2017 (ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል የዜጎችን የሥራ ፈጠራ ክህሎት የማጎልበትና የስራ እድል የመፍጠር ተግባራት በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በመቀሌ ከተማ ዛሬ በተጀመረው ስልጠና ላይ ከ400 በላይ ወጣቶችና ሴቶች እየተሳተፉ መሆኑም ተገልጿል።

በኢንስቲትዩቱ የትግራይ ክልል አስተባባሪ አቶ ዳግማዊ ዮሃንስ እንደገለፁት፤ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች በስራ ፈጠራ ንድፈ ሀሳብ ዙሪያ እና በሙያ ዘርፎች ለወጣቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ ነው። 

ስልጠናውን የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና እና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ እንዲሁም ከትግራይ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ  ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። 

ኢንስቲትዩቱ የስራ ፈጠራ ንድፈ ሀሳብና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለወጣቶች እንደሚሰጥ አመልክተው፤ በተለይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የብድርና የመስሪያ ቦታ የማመቻቸት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ወደ ተግባር ከተገባ ካለፉት ሰባት ወራት ወዲህ ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት አብዛኞቹ ብድር እንዲያገኙ በማድረግ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣቱን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት መንግስት የዜጎችን የስራ ፈጠራ አቅም ለማበረታታትና ለማሳደግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በትግራይ ክልልም የስራ አጥነትን ለመቀነስ ከክልሉ የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና እና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል። 

ሰልጣኝ ወጣቶች ባላቸው እውቀት የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር ከተንቀሳቀሱ አስፈላጊው የብድርና የሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል። 


 

የትግራይ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ሚኪኤለ ሀይለስላሴ በበኩላቸው፤ ወጣቱ በአካባቢው ያለውን የስራ አማራጭና ዕድሎች በስፋት ሊጠቀም እንደሚገባው ገልፀው፤ የስራ ፈጠራንና የንግድ ክህሎትን ለማዳበር የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና መውሰዱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሰልጣኝ ወጣቶች መካከል ወጣት ሳሙኤል ሃደራ፣ በስልጠና የተገኘውን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየርና የንግድ ሥራዎችን  ማከናወን እንደሚጠበቅበት ገልጿል።

''እኔ ከስልጠናው በኋላ ብድር ከተመቻቸልኝ በብረታ ብረትና እንጨት ስራ ዘርፍ የራሴን ስራ ለመፍጠር እቅድ አለኝ'' ብሏል ወጣቱ። 


 

ኢንስቲትዩቱ በአንደኛው ዙር በሰጠው ስልጠና ተሳታፊ እንደነበረች የተናገረችው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ አካል ጉዳተኛ ወጣት አስኳል ግርማይ፤ የ150 ሺህ ብር ብድር እና የመስሪያ ቦታ ማግኘቷን ገልፃለች። 

በንግድ ዘርፍ የራሷን ስራ መፍጠሯን እና ተጠቃሚ መሆኗን በመግለፅ ወጣቱ ከስደት ይልቅ እንደዚህ ዓይነት ዕድል ተጠቅሞ ራሱን መለወጥ እንዳለበት ተናግራለች። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም