ቀጥታ፡

የተ.መ.ድ የብዝኃ-ሕይወት ሥምምነት ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማጠናከር አስችሏል   

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦የተ.መ.ድ የብዝኃ-ሕይወት ሥምምነት ጠቅላላ ጉባዔ (ኮፕ 16) ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ዓለም አቀፍ ትብብሯን ለማጠናከርና ጠቃሚ ልምዶችን ለመቀመር ማስቻሉ ተገለጸ።  

16ኛው የተባበሩት መንግሥታት የብዝኃ-ሕይወት ሥምምነት ጠቅላላ ጉባዔ (ኮፕ 16) ከጥቅምት 11 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በኮሎምቢያ ካሊ ከተማ ተካሂዷል።  

ኢትዮጵያ በስድስት ልዑካን ቡድን አባላት ተወክላ በብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ስትመክር ቆይታለች። 

የኢትዮጵያ ብዝኃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማሪዮ(ዶ/ር) በጉባዔው በተነሱ ጉዳዮችና በተደረሰባቸው ሥምምነቶች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም፤ ኢትዮጵያ በጉባዔው አፍሪካን ወክላም ጭምር ድርድር ስታደርግባቸው እንደነበርና ድርድሮቹም በአብዛኛው ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ብዝኃ-ሕይወትና አየር ንብረት ለውጥ፣ ኃብት ማሰባሰብና ወራሪ መጤ ዝርያዎች ላይ አፍሪካን በመወከል መደራደሯ ተገልጿል።   

በጉባዔው ላይ ከ60 በላይ ሰነዶች ለውሳኔ ቀርበው አብዛኛዎቹ መፅደቃቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ  በብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ላይ እያከናወነች ያለውን ልምድ ከማካፈሏ በተጨማሪ በዘርፉ ከአገራት ልምድ መቀመሯን ጠቅሰዋል።  

በጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ መፅደቁንም አንስተዋል።  

በተጨማሪም በጉባዔው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ላይ የቴክኖሎጂና ቴክኒክ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል የትብብር ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት የብዝኃ-ሕይወት ሥምምነት ጠቅላላ ጉባዔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1994 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም