በክልሉ ስር የሚገኙ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ስር የሚገኙ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ተገለፀ
መቀለ፤ ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስር የሚገኙ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት አስጣጥ ረገድ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመቀለ ቅርንጫፍ ገለፀ።
ቅርንጫፉ ባለፉት ሶስት ወራት በጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚገኙ 39 የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ ባካሄደው ክትትልና ቁጥጥር የተለያየ ዓይነት የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን አግኝቷል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም የመቀለ ቅርንፃፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀሐዬ እምባየ እንደገለፁት፤ በተቋማቱ የተገኘው የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ከእርምት እርምጃ እስከ በህግ እስከመጠየቅ ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ለማህበረሰቡ እየሰጡ ያለውን አገልግሎት እና የተገልጋዩ እርካታ አነስተኛ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚታይባቸው ተቋማት በፍትህ ዘርፍ፤ በማዕድን አስተዳደር፣ በመማር ማስተማር ሂደት እና የጤና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአገልግሎቱ መጓደል ዋና ተብለው የሚጠቀሱ ምክንያቶችም ከአቅም ማነስ፣ ከስነ ምግባር ጉድለት፣ ከግል ጥቅምና ወገንተኝነት የሚመነጩ መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።
እንዲሁም የሰራተኞች ሰዓት አክብሮ በስራ ገበታ ላይ አለመገኘትና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣት ተጠቃሽ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በመቀለና ዓዲግራት ከተሞች ከ33 ሺህ በላይ ካሬ ሜትር ቦታ ያለ አግባብ ለባለጉዳዮች የሰጡ የሥራ ኃላፊዎችም በህግ እንዲጠየቁ መደረጉንም የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አመልክተዋል።
በቀጣይም በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ያለውን ችግር ለመከታተልና እርምጃ ለመውሰድ ተቋማቱ እንዲሰሩም ምክረ ሀሳብ መለገሳቸውን አስረድተዋል።