በድሬደዋ የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ

ድሬደዋ ፤ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦በድሬደዋ የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትግበራ መጀመሩን ምክትል ከንቲባው ሀርቢ ቡህ አስታወቁ።
የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአስተዳደሩ የአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም አሁንም የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለሚቀጥሉት አምስት አመታት አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ በተሻለ ደረጃ የሚለውጠው የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትግበራ መጀመሩ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ አርብቶ አደሩን ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግር ወሳኝ መሆኑን ተናግረው በየደረጃው የሚገኘው የገጠር አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ፕሮጀክቱን ተቀናጅተው ውጤታማ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በድሬደዋ አስተዳደር አራት የገጠር ወረዳዎችና 38 ቀበሌዎች ውስጥ ይተገበራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደር ቤተሰቦችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መመደቡን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ሴቶችና ወጣቶች በተለያዩ የገቢ ማግኛ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት የአፈርና የውሃ ሃብትን በዘላቂነት በመጠበቅ በእንሰሳት ሃብትና በመኖ ልማት ላይ ከፍተኛ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
በተጨማሪም የእንሰሳት ጤና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአነስተኛ መስኖ ስራዎች በፕሮጀክቱ ተካተው ይተገበራሉ ነው ያሉት።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙ የአርብቶ አደሮች ፕሮጀክቱ ከተረጂነት ለመላቀቅ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረቶች ስኬታማ ለማድረግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።