ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች   ደም ለገሱ።

 የተቋሙ ሰራተኞች  ደም የለገሱት ለ14ኛ ጊዜ  ነው።

ከደም ለጋሾች  መካከል  የዜና ማእከል ሃላፊ አቶ ገዛኸኝ ወርቅነህ እንዳሉት  ደም መለገስ በደም እጦት  በተለያዩ ምክንያት የደም እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች  በደም እጦት  ሕይወታቸው እንዳያልፍ መታደግ ነው ።

እኛ በለገስነው ደም የሰውን ሕይወት ማዳን ከምንም በላይ የኅሊና እርካታን    እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል።

ይህን ታላቅ  ማህበራዊ ሃላፊነት በመረዳት ሌሎችም    ተግባሩን እንዲከተሉ ጥር አቅርበዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ጋዜጠኛ የሽመቤት ደመቀ  በበኩሏ ለ11ኛ ጊዜ ደም መለገሷን ገልጻ ደም መለገስ በወሊድ እና በተለያዩ አደጋዎች በሚፈስ  ደም የሚከሰትን ህልፈተ ሕይወት መታደግ መሆኑን  ተናግራለች።


 

በደም ልገሳ ወቅት  ለለጋሹ  ያለ ክፍያ የሚደረጉ የተለያዩ የጤና ምርመራዎችም   ለጋሹ   የጤና ሁኔታውን ለመረዳት እንደሚያግዘውም አክላለች።


 

ላለፉት አስር አመታት በቋሚነት በየሶስት ወሩ ደም  መለገሱን  የገለጸው ደግም ጋዜጠኛ ሙሴ መለስ ነው።

እኔ የምለግሰው ደም የስዎችን ሕይወት ስለሚታደግ በቀጣይም ይህን በጎ ተግባር አጠናክሬ እቀጥላለው ነው ያለው።


 

በተቋሙ  የሴቶችና ባለ ብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር  ታደለች ቦጋለ የሚዲያ ባለሙያዎች ለማኅበረሰቡ መረጃ ከማድረስ በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት አርዓያ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።

ለተግባራዊነቱም  ሰራተኞቹ ደም ልገሳን  ባህል በማድረግ በየሶስት ወሩ ደማቸውን በመለገስ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ  ነው ብለዋል።


 

በዚሁ የደም ልገሳ ፕሮግራም ደም የለገሱት በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ኢዜአ ለተቋማት   በሚሰጠው  የኮሙኒኬሽን ስልጠና በአሰልጣኝነት በተገኙበት አጋጣሚ  በበጎ ተግባሩ  መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የደም ልገሳ  ፍላጎት የማይቋረጥ በመሆኑ በጎ ተግባሩን  በማጠናከር  በደም እጦት ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ዜጎችን ሕይወት እንታደግ ሲሉም   መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።


 

ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት  ይሳቅ ዮናስ ደም በሰዎች ውስጥ በተፈጥሮ ብቻ የሚገኝ ልዩ ስጦታ መሆኑን ጠቁመዋል።

ደም  በየሶስት ወሩ  በተፈጥሮ መልሶ የሚተካና በመለገሳችንም 
ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትልም ተናግረዋል።  

በደም ልገሳ ዙሪያ በማኅበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ገልጸው በተለያዩ ምክንያቶች የደም እጦት የሚያጋጥማቸውን ሰዎች ሕይወት ለመታደግ ደም በመለገስ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን እንወጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።      

                                                                                                                                                                                                    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም