የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር በኩል አፍሪካን ከእስያና ከአውሮፓ ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር በኩል አፍሪካን ከእስያና ከአውሮፓ ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር በኩል አፍሪካን ከእስያና ከአውሮፓ ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአየር መንገዱ የሲንጋፖር፣ የአውስትራሊያና የኒውዝላንድ አካባቢ ኃላፊ ተሊላ ደሬሳ ገለጹ።
አየር መንገዱ የንግድ፣ የጉዞና የባህል ትስስር እንዲሳለጥም ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር ቢሮ ትላንት ማምሻውን በጉዞና በካርጎ(ጭነት) ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ኤጀንቶች እውቅና ሰጥቷል።
በሲንጋፖር በተካሄደው በዚሁ መርኃ ግብር ተሊላ ደሬሳ፤ አየር መንገዱ በሲንጋፖር ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅጾ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጥተናል ብለዋል።
እነዚህ ኤጀንቶች የጉዞ፣ የጭነት(ካርጎ) አገልግሎት፣ ቱሪዝም፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሲንጋፖር መስመር ትርፋማና በእስያ ካሉት መስመሮች መካከል ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት።
ይህም ስኬት ያለ አጋር አካላት ድጋፍና አስተዋጽዖ ሊሳካ እንደማይችል ገልጸው ለኤጀንቶቹ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ሲንጋፖር የቀጥታ በረራ እንዳለው አንስተው ይህም ትስስርን በማሳለጥ የቢዝነስና የባህል ግንኙነትን ለማጎልበት አግዟል ብለዋል።
አየር መንገዱ ሁሉን አቀፍ የአየር አገልግሎት ከአፍሪካ ወደ እስያና አውሮፓ እንዲሁም ከእስያና አውሮፓ ወደ አፍሪካ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ኢቲ ሆሊደይ" ሃላፊ ፍሬህይወት መኮንን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር ማዕከል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል።
ለአብነትም አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የጉዞ ወኪሎችና የካርጎ ኤጀንቶችን አንስተዋል።
ይህንን ተከትሎ በሲንጋፖር ያለው ገበያ እያደገ መምጣቱን በመጥቀስ አጋር አካላቱ ለሰሩት ሥራ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ለአጋር አካላቱ የተሰጠው እውቅና በቀጣይ ከአየር መንገዱ ጋር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ግንባር ቀደም ተቋም ነው።
በመርኃ ግብሩ የተገኙ መንገደኞች፣ የጉዞና የካርጎ ኤጀንቶች አየር መንገዱ በሚሰጠው አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ከአየር መንገዱ ጋር ያላቸውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህም አየር መንገዱ በተፋጠነ የስኬት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት እርምጃ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሳይ ቱሉስ ተነስቶ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
"Ethiopia Land of Origin" የሚል ስያሜ የተሰጠው ግዙፍ፣ ምቹና እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ወደ ናይጀሪያ ሌጎስ እንደሚያደርግም ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።