ቀጥታ፡

የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል ፖሊሲ ሥራ ላይ ውሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል ፖሊሲ ሥራ ላይ ማዋሏን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስተኛውን የሳይበር ደኅንነት ወር ምክንያት በማድረግ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት አድርጓል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርአያሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሳይበር ጥቃት ሥጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ሥጋቱን በአግባቡ መመከት የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም የሚረዳ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ህሊና በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉ፣ የባለሙያዎችና የቴክኖሎጂ እጥረቶች ፈተና መሆናቸውን ጠቁመው ፖሊሲው መሰል ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔዎችን የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

ፖሊሲው በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ እንዲሁም የሕግ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው ባንኩ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ከሲስተም ዝርጋታ በተጨማሪ ለባለሙያዎችና የሥራ ሃላፊዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑንም አንስተዋል።

የሳይበር ደኅንነት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመከላከል በጋራና በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ወር በዓለም ለ21ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም