በአዳማ ከተማ በ94 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ በ94 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ ነው
አዳማ፤ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)- - በአዳማ ከተማ ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ በ94 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተስፋዬ፣ በከተማው የተማሪዎች ምገባ በተደራጀ መልኩ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ ላይ መሻሻል እየመጣ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በተለይም ከችግረኛ ቤተሰብ የሚመጡ ተማሪዎች በሙሉ ሀሳባቸው ትምህርት ባለመከታተላቸው ክፍል መድገምና ማቋረጥ በርከት ብሎ ይስተዋል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
እየተደረገ ያለው ድጋፍ በምግብ ብቻ እንዳልተወሰነና ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑ የወላጆችንም ጭንቀት በእጅጉ የቀነሰ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመትም የተማሪዎች ምገባን በከተማው ባሉ 96 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ከከተማው ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ሳምንትም በ94 የአዳማ ከተማ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ሙሉ በሙሉ መጀመሩን አቶ ደረጀ ገልፀዋል፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት በአዳማ ከተማ የምገባ ስርዓቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ያሉ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡
የምግብ ግብአቶችን የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንና በተቀሩትም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡
በትምህርት ቤት ምገባው በአጠቃላይ ከ47 ሺህ በላይ የከተማው መንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ ቡሳ ጎኖፋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዋዶ አብዱልከሪም፣ ለምገባው የሚውል ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በየትምህርት ቤቱ ለስድስት ሴቶች በምግብ አብሳይነት የስራ እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
የተጀመረውን በጎ ተግባር ዳር ለማድረስ የከተማው ባለሀብትና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ዋዶ ጥሪ አቅርበዋል፡፡