ኢትዮጵያ የቡና ምርት እና ባህሏን በኮሪያ ሪፐብሊክ በተካሄደ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ላይ አስተዋወቀች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የቡና ምርት እና ባህሏን በኮሪያ ሪፐብሊክ በተካሄደ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ላይ አስተዋውቃለች።

‘Seoul International Cafe Show’ የተሰኘው ዓመታዊ አውደ ርዕይ ሴኡል በሚገኘው ኮኤክስ የኤግዚቢሽን ማዕከል ትናንት ተጀምሯል።


 

በአውደ ርዕዩ ላይ ሴኡል የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ ቡና ማህበር በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን ቡናና ባህል በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

ለኢትዮጵያ በተዘጋጀው የአውድ ርዕይ ቦታ ለጎብኚዎች የኢትዮጵያን ባህላዊ ቡና አፈላል ስነ ስርዓት ከተፈጥሯዊው የቡና ቃና ቀለል ካሉ የኢትዮጵያ መገለጫ ከሆኑ ምግቦች ጋር ቀርቦላቸዋል።

በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ አውደ ርዕዩን የጎበኙ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና ማህበር ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ጀና እና ከቡና ላኪዎች ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ደሴ የኢትዮጵያን ቡና ወደ አገራቸው የሚያስገቡ ኩባንያዎች የአውደ ርዕይ ስፍራ ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት ከአያንቱ ኮፊ እና ከሌሎች የቡና ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ሴኡል የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

”Seoul International Cafe Show” የተሰኘው ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም