የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የፋሲል አብያተ መንግሥታት ዕድሳት ቀን ከሌሊት እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የፋሲል አብያተ መንግሥታት ዕድሳት ቀን ከሌሊት እየተፋጠነ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017 (ኢዜአ)፡- የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የፋሲል አብያተ መንግሥታት ዕድሳት ቀን ከሌሊት እየተፋጠነ መሆኑን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በጎንደር ከተማ የተጀመሩት የፋሲል አብያተ መንግሥታት ዕድሳት፣ የኮሪደር ልማትና የጎንደር አዘዞ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛሉ።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች የፋሲል አብያተ መንግስታት ዕድሳትና በመጀመሪያ ዙር ከመስቀል አደባባይ እስከ ጃንተከል ዋርካ እየተፋጠነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ስራ ትናንት ምሽት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው በምሽት ጭምር የሚከናወኑ የኮሪደር ልማትና የአብያተ መንግሥታት እድሳት ስራዎች 24 ሰዓት በመስራት ውጤት የማስመዝገብ የሥራ ባህል ለውጥን ማምጣታቸውን ገልጸዋል።
የአብያተ መንግሥታት ዕድሳትና የኮሪደር ልማቱ ሥራ ቀን ከሌሊት እየተፋጠነ መሆኑን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፥ በሥራው እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞችን አመስግነዋል።
በሁለተኛ ዙርም ከፒያሳ እስከ አየር ማረፊያ ድረስ 14 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራን ማከናወን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የጎንደር የኮሪደር ልማት የከተማዋን የቀደመ ታሪክ ታሳቢ በማድረግ ውብ ገጽታን ማላበስ የሚያስችሉ የህንፃ ዕድሳት፣ የመንገድ ዳር መብራት፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና ብስክሌት መንገዶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።