ቀጥታ፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽህፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2017 (ኢዜአ)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አዲስ ከተሾሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅች የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣የአደገኛ ዕፅ ዝውውር፣ የሀሰተኛ መድኃኒት ዝውውርን፣ የህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን፣ የኮንትሮባንድ ንግድ እና በሙስና ከአገር የሚሸሽ ገንዘብን በመከላከል ረገድ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ከላይ በተገለጹት እና ለቀጣናው ስጋት ደቃኝ ወንጀሎች ዙሪያ ከተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽህፈት ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ዳይሬክተሯ አሺታ ሚታል በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ማለት በቀጣናው ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ጽህፈት ቤታቸውም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የየዘርፉ የኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም