ኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ እየሠራች ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ እየሰራች እንደምትገኝ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተካሄደው የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ፣ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማዳት መሀመድ አህመድ፣ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የናይጀሪያ አምባሳደር ቪክቶር አዴኬሌ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሰው እንየው እና የስፖርቱ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ በስፖርት ዘርፍ ብዙ በመስራት ጤናማ፣ ተወዳዳሪ እና አምራች ማኅበረሰብ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ እና የስፖርት ስልጠናዎችን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ እየሰራች መሆኑን ጠቁመው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችን ታያላችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን እንድታስተናግድ እና ውድድሩን በስኬት እንድታጠናቅቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

መንግስት የእጅ ኳስ በኢትዮጵያ እንዲያድግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማዳት መሀመድ አህመድ ይህን ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንዲካሄድ የወሰነው ኢትዮጵያ በእጅ ኳስ ውድድር እያሳየች ያለውን መሻሻል እና ውድድር የማስተናገድ አቅሟን በማየት ነው ብለዋል።

በትክክልም ኢትዮጵያ የስፖርት ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት አይተናል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን በማስተናገድ በዓለም የምትታወቅበትን እንግዳ ተቀባይነት ለተሳታፊ ሀገራት ማሳየቷን ገልጸዋል።

ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ ገፅታ የተገነባበት፣ ውድድርን የማስተናገድ አቅሟ ጎልቶ የታየበት እና ኢትዮጵያም በውድድሩ ብርቱና ተፎካካሪ መሆኗን ያስመሰከረችበት መሆኑን አመልክተዋል።

በዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ናይጄሪያ ከ18 ዓመት በታች እንዲሁም ሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች አሸናፊ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ውድድር አራተኛ ስትወጣ ከ20 ዓመት በታች ውድድሩ ላይ ተሳትፎ አላደረገችም።

“ስፖርት ለአህጉራዊ ሰላም” በሚል ሀሳብ የተካሄደው ሻምፒዮና የተዘጋጀው በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን፣ በአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና በዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጋራ ትብብር መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም