ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂው ዳዊት ገብሩ በ59ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን መሪ አድርጎ ነበር።

የፊት መስመር ተሰላፊው አዲስ ግደይ በ71ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት እና በ73ኛው ደቂቃ በጨዋታ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸው ግቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሶስት ነጥብ ባለቤት አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰ ሲሆን በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አሳክቷል።

ቡድኑ በሰባት ነጥብ ከነበረበት 16ኛ ደረጃ ወደ 12 ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል።

በአንጻሩ በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ስድስተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ቡድኑ ያለ ምንም ነጥብ ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።

የዛሬ ጨዋታዎችን ተከትሎ የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።

ፕሪሚየር ሊጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ታንዛንያ በሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት እንደሚቋረጥ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ሊጉ ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም በስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወደ ውድድር እንደሚመለስ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም