የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማ የዶሮ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማ የዶሮ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት እየሰራ ነው

ፅፅቃ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማ የዶሮ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የምርምር ማዕከሉ "ሬስ ኤፍ ኤስ" ከተባለ ፕሮጀክት ባገኘው ድጋፍ በዞኑ ዝቋላ ወረዳ በእንቁላልና በሥጋ ዶሮ እርባታ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን አርሶ አደሮች የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ ተደርጓል።
በሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል የማህበራዊ ምጣኔ ሃብትና ግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ አቶ አደመ ምህረቱ እንዳሉት፣ ማዕከሉ ለቆላማ ወረዳዎች ተስማሚ የሆነ "ሳሶ" የተባለ የዶሮ ዝርያ እያቀረበ ነው።
በዝቋላ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ 20 አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው 50 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማቅረብ እንቁላልን ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲያቀርቡ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብር በማሳተፍ በምግብ እራስን ለመቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ነው።
ለዚህም የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
ይህም እናቶች በዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርተው ልጆቻቸውን የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ የህጻናትን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
ማዕከሉ ከአትክልት በተጨማሪ የእንቁላልና የዶሮ ሥጋ ልማትን በማስፋፋት ስርዓተ ምግብን ለማሻሻልና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት የጀመረው ተግባር አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በዝቋላ ወረዳ የቀበሌ 01 ነዋሪ ወይዘሮ ፈትለ አየለ በበኩላቸው በማዕከሉ ከቀረበላቸው 50 የእንቁላል ጣይ ደሮዎች በቀን ከ40 በላይ እንቁላል እያገኙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የደሮ ሥጋና እንቁላል ልማት ሥራቸውን በቀጣይም በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በእንቁላልና በሥጋ ምርታማ የሆኑ ዶሮዎችን ማርባት በመቻላችን ተጠቃሚ አድርጎናል ያሉት ሌላው የፅፅቃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ጊብቱ ናቸው።
በዛሬው እለት በከተማው በተካሄደ የመስክ ምልከታ የብሔረሰብ አስተዳደሩ እና የግብርና ምርምር ማዕከላት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ተመራማሪዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።