አፍሪካ የቱሪዝም ኃብትን ለዘላቂ ምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና አሟጣ መጠቀም ይገባታል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የቱሪዝም ኃብትን ለዘላቂ ምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና አሟጣ መጠቀም ይገባታል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለዘላቂ ምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና አሟጣ መጠቀም እንደሚገባት ተገለጸ።
አፍሪካ ሰለብሪቲስ 2024 መርኃ-ግብር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
አፍሪካን በትምህርት፣ በጥበብ፣ በባህልና በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የአህጉሪቱን ልማትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማገዝ የተዘጋጀ መርኃ-ግብር ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ጊዜ፤ አፍሪካ በቱሪዝም ዘርፍ ለምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና የሚውል እምቅ አቅም አላት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክና የተለየ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን በመግለጽ፤ የአፍሪካ ሰለብሪቲስ 2024 ይህንን ታሪክና ባህል ለአፍሪካውያን ለማሳየት ያግዛል ነው ያሉት።
አፍሪካ ሰለብሪቲስ አፍሪካ ያላትን የተለያየ ባህል፣ ጥበብና ፈጠራ በአንድ በማስተሳሰር ለልማትና ብልጽግና መጠቀም የሚያስችል ሁነት መሆኑን አንስተዋል።
ቱሪዝም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማፋጠን ያለውን ሚና በመግለጽ፤ አፍሪካን ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቁመዋል።
አፍሪካ ለማኅበራዊና ምጣኔ ኃብት ልማት የሚውል ልዩና አስደናቂ የቱሪዝም መዳረሻ ያላት አህጉር በመሆኗ የአፍሪካ ሰለብሪቲ መሰል መድረኮች ለዓለም ለማሳየት ያግዛል ብለዋል።
ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን ለቱሪዝም መስህብነት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካኒዝም መነሻ እንደመሆኗ በትብብር ቱሪዝምን አልምቶ ለመጠቀም ዝግጁ ናት ብለዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማቲክ መቀመጫ በመሆኗ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀረው ዓለም በማስተሳሰር በሚሰጠው አገልግሎት በስብሰባና በኮንፍረንስ ላይ የተመሠረተ ቱሪዝም(ማይስ ቱሪዝም) መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሰለብሪቲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌክሲ ሞጆ በበኩላቸው፤ ሁነቱ በአፍሪካ የንግድ ልውውጥን፣ የባህልና ሌሎች ትስስሮችን በማጠናከርና የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀዋል።
የፓን-አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ገና በበኩላቸው፤ የፈጠራ ኢንዱስትሪው በዓለም 2 ነጥብ 5 ትሪሊየን ገበያ እንዲሁም 50 ሚሊየን የሥራ ዕድል እንዳለው ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ለፈጠራና ጥበብ በዓመት የምትይዘው በጀት ከ1 በመቶ በታች እንደሆነ በማንሳት ትኩረት እንደሚያሻው ጠቁመዋል።
አፍሪካውያን ያላቸውን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ ለምጣኔ ኃብት እድገት ለማዋል አንድነትን በማጠናከር እርስ በርስ መተዋወቅን ማጠናከር እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ኒያሚቱዬ ናቸው።
አፍሪካ ሰለብሪቲስ 2024 መርኃ-ግብር በአፍሪካ ጥበብ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ከ42 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የምጣኔ ኃብት ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌ መሪዎች፣ ንግስቶች፣ ንጉሶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የቱሪዝም ተዋናዮችና ሌሎች ተገኝተዋል።
መርኃ-ግብሩ ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የአፍሪካን ምርቶች የሚያሳይ አውደ-ርዕይ፣ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም፣ ጉብኝትና ሌሎች ሁነቶች ይካሄዱበታል።