የኢትዮጵያን ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አቅም ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ወደ ሥራ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አቅም ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ወደ ሥራ ገባ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ መሠረታዊ የምልከታ አውታር ፕሮጀክት ወደ ስራ ገብቷል።
ፕሮጀክቱ በ9 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ለሦስት ዓመታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የአየር ሁኔታ መከታተያ ጣቢያ በማቋቋም የምትሰበስባቸውና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምታጋራቸው የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ አሁን ሥራ ላይ የሚገኙ ለዓለም አቀፍ መረጃ ልውውጥ እያገለገሉ ያሉ 16 ጣቢያዎች የገፀ-ምድር በሰው የሚሠሩ የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰው አልባ(አውቶማቲክ) የማሳደግ፣ እንዲሁም መረጃ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ተጨማሪ 13 አዳዲስ የገፀ-ምድር አውቶማቲክ የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎችን ማቋቋምን ያካትታል ተብሏል።
በተጨማሪም፤ ሁለት የከፍታ አየር የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያን ማደስና ተጨማሪ ሦስት አዳዲስ የከፍታ አየር ጣቢያን ማቋቋምን ይጨምራል ተብሏል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፤ ፕሮጀክቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና የአይ.ሲ.ቲ. መሣሪያዎች ማሟላትን እንደሚጨምር ተናግረዋል።
መረጃዎችን ያለማቋረጥ በመሰብሰብና ለዓለም በማጋራት፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ከመላው ዓለም የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በመቀበልና በመተንተን የአየር ሁኔታ መረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ፣ በአህጉርና ሀገራዊ የአየር ትንበያ ሞዴሎች ውስጥ መረጃዎቹ እንዲካተቱ በማድረግ የትንበያ ትክክለኛነትና ጥራት ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ተጓዳኝ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመጥቀስ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን እንዲያጠናክር ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑንም አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፤ ከኢንስቲትዩቱ የሚገኘው መረጃ ሀገር ለምታከናውናቸው ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትክክለኛ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለተረጋጋና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።
የተ.መ.ድ የልማት መርኃ-ግብር(ዩ ኤን ዲ ፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው፤ የተያዘው ፕሮጀክት እንዲሳካ ድርጅቱ ይደግፋል ብለዋል።
በዚህም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የኢንስቲትዩቱን አቅም ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅበትን ተግባር እንዲወጣ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።