ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይና ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲ የቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ልዑክ አባላትን ተቀብለው አነጋግረዋል።


 

የልዑክ ቡድኑ መሪ ጆን ጂልስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በሰፊው የሚገኙባት ሀገር መሆኗን ገልጸው ይህን የኢንቨስትመንት ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በቻይና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤትም ይህንን እውነታ ከግምት በማስገባት በመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም ከ300 በላይ ከአፍሪካ እና ከእስያ የተውጣጡ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

አቶ ዘመን ጁነዲ ኮርፖሬሽኑ የቻይና ባለሀብቶችን ለመሳብ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቤጂንግ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና አዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የቻይና አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት አባላትም ይህንኑ እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም