ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር መልክና ልክ- ጀፎረ

የገጠር ኮሪደር መልክና ልክ- ጀፎረ                     

በዚህ መንደር ተፈጥሮና ተለምዶ ተሰባጥረዋል፤ የኑባሬ በይነ-ፈርጆች ተዋደዋል። ይህን ለዕይታ ማራኪ፣ መንፈስን በሐሴት አርኪ፣ በተመስጦ ቀልብ ወስዋሽ፣ ትሩፋተ-ብዙው ለምለም ቀዬ፤ ዘመነኛ ጥበበኛ መሃንዲስ አልቀየሰውም። 

የዘመናችን የአካባቢ ስነ-ውበት ባለሙያ አልተጨነቀበትም። የምትሃተኛ ኪነ-ህንፃ ባለሙያ፣ የዝነኛ የገጸ- ምድር ንድፈኛ ውጤት አይደለም። ዘመናዊ የሥርዓተ-ምኅዳር ሳይንቲስቶች አሻራም አላረፈበትም።

ሥሪቱም፣ መሠረቱም፣ ትዕምርቱም የጥንት የጥዋት ነው። የሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ማሳያ። ምዕተ- ዓመታት የተሻገረ የትውልድ ቅርስም፣ ውርስም።

የሀገረ-ስዊዘርላንድ ውድ መንደሮችን የሚያስንቀው ይህ ውብና ፅዱ መንደር፣ የጉራጌዎች ጀፎረ ነው። 

በዘመናት ዑደት ውስጥ ከነግርማ ሞገሱ የተሻገረ የጉራጌ መንደሮች ባህላዊ ጎዳና፣ የትውፊታዊ ትዕይንቶች መድረክ ነው። 

ባለሐመልማላዊ ገጹ ጀፎረ ለጉራጌ ማኅበረሰብ አንዱ መልክና ልክ፤ ግልጋሎቱም አድማስ ሰበር እና ዘመን ዘለል ነው።

በአባቶች ተረክ ጀፎረ ከሥራ ወዳዱ የጉራጌ ጥንተ-ማኅበረሰብ ዘንድ በንግድ እንቅስቃሴ ሂደት ተወጥኖ ከወትሮ እስከ ዘንድሮ ዘልቋል። 

ጀፎረ ውበትና ጌጥ ብቻ አይደለም። ትውፊታዊ መልክና ግልጋሎቱ ፈርጀ-ብዙ ነው። በዘፈቀደ የሚሰመር ሳይሆን የራሱ የአሰማመርና የልኬት ስልት ይመራል።

እናም ጀፎረ ተራ ጎዳና ሳይሆን የአካባቢው ተወላጆች ከልጅነት እስከ ዕውቀት ማንነት የሚቀረጽበት የሕይወት ጎዳና ነው - ሁለንተናዊ መልህቅ።


 

ለዚህ ምስክሩ ደግሞ በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ከእምድብር ከተማ በስተምዕራብ አስተኮ ቀበሌ የሚገኘው የጠናቃ ጀፎረ መንደር የተወለዱት ብርሃኔ ዘለቃ ናቸው።

የዛሬው የዕድሜ ባለጸጋ በልጅነት የቦረቁት፣ በወጣትነት የዘለሉት፣ በጎልማሳነት ቁም ነገር የቀሰሙት፣ በማምሻ ዕድሜያቸው የተድላ ሕይወት የሚመሩት በጀፎረ ጎዳናዎች ነው።

ጀፎረ በጋሽ ብርሃኔ ገለፃ ጆፎሮ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ትዝታ ስንቃቸው፣ በሕይወት ሁለንተናቸው ነው።

የጉራጌ ማኅበረሰብ ተናፋቂው የመስቀል በዓልን ጨምሮ የወል በዓላት ይዘከሩበታል። እናም ለጋሽ ብርሃኔና መሰሎች የቀዬው ተወላጆች ውበትም፣ ሕይወትም ነው።

ጀፎረ ለማኅበራዊ ትውፊቶች የክዋኔ ሥፍራ፣ የብስራትም የመርዶም መንገሪያ፣ የሰርግም የተስካርም ሁነቶች መከወኛ፣ ጥቁር እንግዳ መቀበያ፣ ሰንባች እንግዳ መሸኛ፣ እረኞች ከብት የሚወስዱበትና የሚመልሱበት፣ የወል ኃብት ነው።

ሌላው የሥፍራው ተወላጅ አቶ ተሾመ ቸሩ በበኩላቸው፤ ጀፎረን “ከቀደምት ጥበበኛ አባቶች የወረስነው እና ዛሬም የምንኖረው ታላቅ ቅርሳችን” ይሉታል።

ጀፎረ ትንሹም፣ ትልቁም የማኅበረሰብ ክፍል ያለምንም የመደብ ልዩነት በእኩልነትና በጋራ የመጠቀም መብት የሰጠ በመሆኑም የፍትህና የእኩልነት ምልክት ይሉታል።


 

የየጆካ ቂጫን ጨምሮ የዳኝነት ሥርዓቶች የሚከወኑበት፣ የውይይትና ምክክር መድረክ ነው-ጀፎረ። የተጣሉ ነዋሪዎች የሚታረቁበት በመሆኑም የጥል ማስወገጃ፣ የሰላም ማንበሪያ ሥፍራ ይሉታል። 

ውብ ተፈጥሮ የተጠበቀበት ንጹህ አየር የሚነፍስበት ነውና ጀፎረ ለጤናማ ኑሮ መሠረት ሆኗል።

በጀፎረ አፈር መቆፈር፣ አንድ ስንዝር ወደፊት ገብቶ ማጠር፣ ቆሻሻ መጣልም ሆነ ሌሎች ደንቦችን መጣስ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተወገዘ ተግባር ነው።

በዚህም ጀፎረ ለሁሉም የሚያገለግል፤ በሁሉም የሚጠበቅ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ የልክነት፣ የሥርዓት አክባሪነት መገለጫም ጭምር ሆኗል።

ለጉራጌ ማኅበረሰብ ሁለንተና የሆነው ጀፎረ፤ ከዚህ መልክና አገልግሎቱ ባሻገርም ለፅዱና ጤናማ አካባቢ መፈጠር እንደ አብነት ይወሰዳል። 

ፅዳትና ውበት ብቻም ሳይሆን ጎዳናውን ተከትለው በተገነቡ መኖሪያ ቤቶች የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ አይታጣም።

የቤቶቹም የኑሮ ጥራትም በየጊዜው እየዘመኑ በመምጣት ፅዱና ጤናማ ህይወት ለመምራት መሠረት ሆነዋል። እናም ጀፎረ ዕውቀትም፣ ውበትም፣ ሲሳይም አቀናጅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ያስጀመሩትን የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ መገለጫ የዘመኑ የገጠር ኮሪደር መነሻም፣ መድረሻም የሚሆን መልክም፣ ልክም ነው።

የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ ውብና ጤናማ የገጠር ከባቢ በመፍጠር የተሟላ ብልጽግና ለማረጋገጥ ብዙ ልፋት የማይጠይቅ ቀድሞ የተዘጋጀ መደላድል ነው-ጀፎረ።

ሌላው ከጀፎረ ቁልፍ አበርክቶዎች መካከል ለመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ያለው ምቹነት ነው።

ጀፎረ መኖሩ በመንደሮች መሃል የውኃ፣ የመብራት፣ የመንገድና ሌሎች መሠረተ-ልማቶችን ያለምንም የወሰን ማስከበር ውጣውረድ ማከናወን ይቻላል።

በዚህም አካባቢው የመብራት አገልግሎትን ጨምሮ በቀላሉ ለዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን እንዳስቻለው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎችና ከተሞችም የጀፎረን ጥበብ ቢከተሉ ለጤናማ፣ ፅዱና አረንጓዴ አካባቢ ግንባታ እንደሚበጅ ያነሳሉ።


 

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምነሳ፤ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት በጉራጌ ማኅበረሰብ የተለመደና የሚኖር እሴት መሆኑን ገልፀዋል።

ጀፎረ የማኅበራዊ ሁነቶች እንዲሁም የመንግሥታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚስተናገድበት ሥፍራ መሆኑን በመጥቀስ፣ እየሰጠ ያለውን ፈርጀ-ብዙ ፋይዳ አንስተዋል። 

ከጀፎረ ጋር ተያይዞ የአትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የፅዱ አካባቢ እና የባህል ይዘቱን ጠብቆ የማስቀጠል የተቀናጀ አሠራር ገቢራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ያስጀመሩትን የገጠር ኮሪደር ልማት በተግባር ለመኖር ቀድሞ የተነሳ ወጣት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም