ቀጥታ፡

የጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ በዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ሻምፒዮና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ የጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ሻምፒዮና የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በአካዳሚው አቀባበል አድርገውላቸዋል።


 

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የስፖርት ማህበራት ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና (IHF Trophy Africa) ከጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቷል።

ሻምፒዮናውን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል።

ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እህትማማች ሀገሮች መካከል የመቀራረብ፤ የመተዋወቅ እና የመደጋግፍን ባህል ለማዳበር አስተዋጽኦ እንዳለው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም