በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የተዘጋጁ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የተዘጋጁ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

5ኛው ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።

አውደ ርዕዩ ደረጃ ኢንፎማይንድ ሶሉሽን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በመርኃ ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች።


 

የሰው ኃብት ለሀገር ልማት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ገልጸው ይህንንም በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ መምራት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

ባለፉት አመታት በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የተዘጋጁ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው መሰል መድረኮች በየጊዜው መዘጋጀት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ጎን ለጎንም ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የሥራ ባህልን ማጠናከር ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ኃላፊ ሳሙኤል ያለው፤ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


 

በዘርፉ የተገኙ ውጤቶች በተጠናከረ አንድነትና በትብብር በመሥራት የተገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የደረጃ ኢንፎማይንድ ሶሉሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሱፍ ረጃ አውደ ርዕዩ የሥራ ዕድል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላለው የሥራ አጥነት ችግር መፍትሄ ይዞ መቅረብን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አውደ ርዕዩ ሥራ ፈላጊዎች በቀጥታ ከቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙበት መድረክ የተዘጋጀበትና በክፍት የሥራ ቦታዎች ምልመላ የሚደረግበት መሆኑንም አመላክተዋል።

በአውደ ርዕዩ 300 የሚሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ በተለያዩ መስኮች የስራ እድሎች የሚፈጠርበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም