ቀጥታ፡

በአፍሪካ የቱሪዝም ኃብትን ለዘላቂ ምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና አሟጦ መጠቀም ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለዘላቂ ምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ። 

አፍሪካ ሰለብሪቲ 2024 መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።   

አፍሪካን በትምህርት፣ በጥበብ፣ በባህልና በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የአህጉሪቱን ልማትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማገዝ የተዘጋጀ መርኃ ግብር መሆኑም ተመላክቷል። 

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ጊዜ፤ አፍሪካ በቱሪዝም ዘርፍ ለምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና የሚውል እምቅ አቅም አላት ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክና የተለየ ባህል ያላት አገር መሆኗን በመግለፅ የአፍሪካ ሰለብሪቲስ 2024 ይህንን ታሪክና ባህል ለአፍሪካውያን ለማሳየት ያግዛል ነው ያሉት። 

የአፍሪካ ሰለብሪቲስ አፍሪካ ያላትን የተለያየ ባህል፣ ጥበብና ፈጠራ በአንድ በማስተሳሰር ለልማትና ብልጽግና መጠቀም የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ቱሪዝም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማፍጠን ያለውን ሚና በመግለጽ አፍሪካ ከአለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቁመዋል።  

አፍሪካ ለማኅበራዊና ምጣኔ ኃብት ልማት የሚውል ልዩና አስደናቂ የቱሪዝም መዳረሻ ያላት አህጉር በመሆኗ የአፍሪካ ሰለብሪቲ መሰል መድረኮች ለዓለም ለማሳየት ያግዛል ብለዋል። 

ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን  ለቱሪዝም መስህብነት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ እንደመሆኗ በትብብር ቱሪዝምን አልምቶ ለመጠቀም ዝግጁ ናት ብለዋል።

የአፍሪካ ሰለብሪቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌክሲ ሞጆ በበኩላቸው በአፍሪካ የንግድ ልውውጥን፣ የባህልና ሌሎች ትስስሮችን በማጠናከርና የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድረግ በየአመቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአፍሪካ በጥበብ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ላይ ባተኮረው በዚህ መርኃ ግብር ከ42 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የምጣኔ ኃብት ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ንግስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የቱሪዝም ተዋናዮችና ሌሎች ተገኝተዋል። 

የአፍሪካ ሰለብሪቲ መርኃ ግብር ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካን ምርቶች የሚያሳይ አውደርዕይ፣ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ውይይቶች፣ ጉብኝትና ሌሎች ሁነቶች ይካሄዱበታል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ)ና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም