የሌማት ትሩፋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና እያቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና እያቃለለ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና እያቃለለ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የግብርና ምርምር ማዕከላት በምርምር የተደገፉ ምክረ-ሀሳቦችን በማቅረብና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማፍራት ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
ለዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ በማድረግ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጀመሩ ይታወቃል፡፡
በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የዶሮና እንቁላል፣ የወተትና ሥጋ እንዲሁም የማር ምርት መንደሮች ተደራጅተው ምርት ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከሁለት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአራት ዓመት የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ከወዲሁ ግቡን አሳክቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ከመጀመሩ በፊት በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ሊትር የነበረው የወተት ምርት በ2016 ዓ.ም. 10 ቢሊየን ሊትር ደርሷል ብለዋል፡፡
በተያዘው የ2017 ዓ.ም የወተት ምርቱን 12 ቢሊየን ሊትር ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም አጠቃላይ የእንቁላል ምርት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፈው ዓመት ከ5 ነጥብ 7 ቢሊየን መሻገሩን ተናግረዋል፡፡
የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች፣ የሥጋና እንቁላል የዶሮ ጫጩቶች እንዲሁም ሌሎች የሌማት ትሩፋት ምርቶች በእጥፍ እያደጉ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀደውን ዕቅድ ቀድሞ ማሳካት መቻሉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መርኃ-ግብሩ በወተት፣ እንቁላል፣ ማር እና ሌሎችም ዘርፎች የተትረፈረፈ ምርት ማምረት አስችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም ምርቶችን በተለያዩ ምክንያቶች የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ የሌማት ትሩፋት ውጤቶች የዋጋ መረጋጋት የታየባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ምርቶች የገበያውን ዋጋ በማረጋጋት በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና እያቃለሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የግብርና ምርምር ማዕከላት በምርምር የተደገፉ ምክረ-ሀሳቦችን በማቅረብ እና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት ለሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ሌሎችም የምርምር ተቋማት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡