በመቻቻልና በመደማመጥ ከተወያየን ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮች መፍቻ ቁልፉ በእኛው እጅ ላይ ነው -ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው - ኢዜአ አማርኛ
በመቻቻልና በመደማመጥ ከተወያየን ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮች መፍቻ ቁልፉ በእኛው እጅ ላይ ነው -ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው
ቦንጋ፤ጥቅምት 27/2017 (ኢዜአ)፦በመቻቻልና በመደማመጥ ከተወያየን ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮች መፍቻ ቁልፉ በእኛው እጅ ላይ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው ገለጹ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተጽዕኖ ፈጣሪዎች አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገዬ አስፋው፥ በክልሉ ባለፉት ቀናት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል።
በዛሬው ዕለትም የተለያዩ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደሀገር በተለያዩ ጊዜያት የተስተዋሉ ግጭቶች መንስኤያቸውን ለይቶ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለመገንባት ምክክሩ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም፥ ለዘመናት ቅራኔ ሲፈጥሩ የነበሩ የቆዩ ችግሮችን ሁሉን ባሳተፈ መንገድ በውይይት መፍታት ወሳኝ ነው።
በመሆኑም፥ በመቻቻልና በመደማመጥ ከተወያየን ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፍቻ ቁልፉ በእኛው እጅ ላይ ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎች ያለምንም ስጋት ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ሀገራዊ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እስካሁን የማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም የአጀንዳ ልየታና የማሰባሰብ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በህብረተሰቡ ውስጥ መተማመንን ለመፍጠርና የውይይት ባህልን ለማዳበር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በመድረኩ በቀጣይ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን የመምረጥ ሥራም እንደሚከናወን ታውቋል።