በቁጭት የጀመርነውን ልማት የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የማድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በቁጭት የጀመርነውን ልማት የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የማድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2017(ኢዜአ)፦ በቁጭት የጀመርነውን ልማት የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የማድረስ ግስጋሴያችንን እናፋጥናለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአራት ቀናት የማሌዢያ ቆይታችን ኳላ ላምፑር፣ ሳይበርጂያ እና ፑትራጂያ የተባሉ ከተሞቻቸውን ጎብኝተናል ብለዋል።
በቆይታችን ነባር ከተሞቻቸውን ከማደስ በተጨማሪ አዳዲስ ከተሞችንም እየገነቡ መሆኑን መመልከታቸው ገልጸው ።
ነባሮቹም ሆኑ አዲስ የሚገነቡ ከተሞቻቸውን ልዩ የሚያደርጋቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸውና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚገለገሉባቸው ሰፋፊ የህዝብ መዝናኛዎችን፣ የኮንቬንሽንና የገበያ ማዕከላትን፣ መናፈሻዎችን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባታቸው ጠቅሰዋል።
ሰው ሰራሽ ወንዝ እና ሃይቆች በመፍጠር ንጹህ ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን መገንባታቸው እንዲሁም ከአጠቃላይ የከተማው ስፋት 38 በመቶ የሚሆነውን ለአረንጓዴ ልማት በማዋል ትልቅ ስራ መስራታቸውም ገልጸዋል።
የሚገርመው ይህም በቂ አይደለም በማለት፣ ስራው እንደ ቅንጦት ሳይሆን ከመታመም በፊት መከላከል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ እና የጤና አጠባበቅ ወሳኝ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉ ሲሉም ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ዘግይተንም ቢሆን የጀመርነው ስራ እየፈጠነ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ እኛ ከእነሱ አንፃር በተሻለ ሁኔታ ክረምትና በጋ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ የማያስፈልገው፣ ወጥነት ያለው ተስማሚ የአየር ንብረት እና ውሃ፣ ትልቅ የሰው ሀይል እንዲሁም ሰፊ መሬት ያለን ሲሆን ይህን እምቅ አቅማችንን በመጠቀም ከተማችንን ለመለወጥ በመስራት ላይ እንገኛለን ሲሉም አብራርተዋል።
በተለይ በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋናችን በአምስት ዓመት ውስጥ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማድረስ ችለናል ብለዋል።
ህዝባችንን በማስተባበር በጀመርነው የ24/7 የስራ መርሃግብር የከተማችንን ነዋሪዎች ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነውን ንጹህ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢ መፍጠርን፣ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ክፍት ቦታዎችን ማዘጋጀትን፣ ለእግረኛ መንገዶች ትኩረት በመስጠት ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች መገንባትን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
በተጨማሪም ፓርኮችን እና መናፈሻዎችን ማስፋፋትን፣ የአረንጓዴ ልማት ሽፋናችንን አሁን ካደረስነው በላይ ማሳደግን፣ የህፃናትና ታዳጊዎች የመጫወቻ ስፍራዎችን ማስፋፋትን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በብዛት መገንባትን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።
ብንዘገይም ገብቶን ጀምረናል፤ አካሄዳችን ትክክለኛ መሆኑንም ከኛ ቀድመው ከተገበሩት ጭምር ተመልክተናል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው በቁጭት የጀመርነውን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የመድረስ ግስጋሴያችን እናፋጥናለን እንጂ ፈፅሞ አንቆምም፤ አንዘገይምም ብለዋል።