5ኛው ሀገርአቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
5ኛው ሀገርአቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ ተከፈተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2017 (ኢዜአ)፦ 5ኛው ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
የአውደ ርዕዩ ደረጃ ኢንፎማይንድ ሶሉሽን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
በመርሐ ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የሰው ሀብት ለሀገር ልማት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው ይህንንም በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ መምራት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ፖሊሲዎች የስራ እድልን በሚፈጥር መንገድ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
በሚኒስቴሩ የበለጸገው ሲስተም አቅርቦት እና ፍላጎት እንዲጣጣም ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የስራ ባህልን ማጠናከር ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።
የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ መሰል መድረኮች በየጊዜው መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ካንትሪ ማኔጀር ሳሙኤል ያለው፥ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የስራ ዕድል ፈጠራ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የደረጃ ኢንፎማይንድ ሶሉሽን መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ የሱፍ ረጃ አውደ ርዕዩ የስራ ዕድል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላለው የስራ አጥነት ችግር መፍትሄ ይዞ መቅረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አውደ ርዕዩ ሥራ ፈላጊዎች በቀጥታ ከቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙበት መድረክ የተዘጋጀበትና በክፍት የስራ ቦታዎች ምልመላ የሚደረግበት መሆኑን አመላክተዋል።
በአውደ ርዕዩ 300 የሚሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከ30 ሺህ በላይ በተለያዩ መስኮች የስራ እድሎች የሚፈጠርበት መሆኑን ተናግረዋል።