19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተደመረ አቅም አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት በሚያስችል መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተደመረ አቅም አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት በሚያስችል መልኩ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2017 (ኢዜአ)፦19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተደመረ አቅም አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት በሚያስችል መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ ኅዳር 29 ቀን የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።
በዓሉ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለብዝኃነት ዕውቅና ለመስጠት፣ እኩልነትን ለማስተናገድ፣ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል።
በዓሉ በሚከበርባቸው ክልሎች መሠረተ-ልማትና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት የሕዳሴውን ግድብ እውን ለማድረግ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል።
ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “አገራዊ መግባባት ለሕብረ- ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ እንደሚከበርም ታውቋል።
የበዓሉን ዝግጅት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ታሪኩ ኦይቻ፤ በዓሉ የአንድነት፣ የሰላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የሕብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ብዙ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴትና የተፈጥሮ መስህብ መኖራቸውን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ያሉ መልካም እሴቶችን በተደመረ አቅም በመማማር አንድነትን ለማጠናከር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
በዓሉ በክልሉ መከበሩ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ከአቀባበል ጀምሮ ሆቴሎች ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና ታዳሚዎችም መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው፤ የእነዚህ ባህል፣ ታሪክና እሴቶችን የመሰነድ፣ የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና የመንከባከብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አርባ ምንጭ ከተማ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ መሆኗን ገልጸው፤በዓሉ በከተማዋ መከበሩ ኃብቶቿን ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማው ለእንግዳ ማረፊያ የሚሆኑ ቦታዎችና የሚጎበኙ መዳረሻዎችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ከወዲሁ የመለየት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ መከበሩ ይታወሳል።