ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ ሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ድሬዳዋ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 10 በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል። ድሬዳዋ ከተማ በስምንት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሶስቱ ሽንፈት ሲገጥመው አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ ቡድኑ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። በግርማ ታደሰ የሚሰለጥነው ሀዲያ ሆሳዕና በአራት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ከምሽቱ 1 ሰዓት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው አምስቱም ጨዋታዎች ሸንፈት ገጥሞታል። 

በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር  ስምንት ግቦችን አስተናግዷል ። ቡድኑ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የውጤት ማጣት ውስጥ የገባው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከክለቡ ማሰናበቱ ይታወቃል። ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በሊጉ እስከ አሁን አራት ጨዋታዎችን አድርጎ  አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ስድስት ጎሎችን አስተናግዷል። በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በአራት ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ጅማሮ አላሳየም።

ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ ፕሪሚየር ሊጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚያደርጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት እንደሚቋረጥ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፋሲል ከነማን ሲያሸንፍ  ኢትዮጵያ ቡና እና ስሑል ሽሬ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም