ቀጥታ፡

መንግስት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ ሰነድ እንዲከፈል መፍቀዱ ባንኩን ጠንካራ መሰረት ለማስያዝ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ ሰነድ እንዲከፈል መፍቀዱ ባንኩን ጠንካራ መሰረት ለማስያዝ የሚያስችል እንደሆነ ተገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አራተኛ ዓመት  የስራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ስብሰባ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን አንድ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

ምክር ቤቱ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።


 

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አዋጁን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስት ልማት ድርጅቶች በብድር የሰጠውን ገንዘብ ወደዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እንዲተላለፍ መደረጉን አስታውሰዋል።  

ኮርፖሬሽኑ ለዕዳው መክፈያ ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ የተመደበለትን ካፒታል፣ ከንግድ ስራ እንቅስቃሴ የሚገኘው ገቢ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች የሚመደብለትን ገንዘብ ይጠቀማል ተብሎ ታቅዶ እንደነበርም ተናግረዋል።

ሆኖም በታቀደው መሰረት ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችል በቂ የገቢ ምንጭ ሊኖር ባለመቻሉ ዕዳው በወቅቱ ሳይከፈል ቆይቶ የወለድ ሂሳቡ የዕዳውን ጫና እያከበደው መሄዱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 845 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሂሳብ ይዞ መቆየቱ በባንኩ የፋይናንስ ገፅታ ላይ አሉታዊ ውጤት በማስከተሉ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ባንኩ በአገሪቱ የባንክ ዘርፍ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ቢሆንም የተፈቀደለት ካፒታል 4 ቢሊየን ብቻ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባንኩ በገበያ ውስጥ ያለውን ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ የተከፈለውን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከባንኩ የወሰዱትን ብድር ለመክፈል ባለመቻላቸው ዕዳውን መንግስት ተረክቦ ክፍያው ለመክፈልና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ በመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲከፈል ለማድረግ 900 ቢሊየን ብር ቦንድ እንዲፈቀድ ረቂቅ አዋጁ መቅረቡንም ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች በፈጠሩት ጫና የባንኩ የፋይናንስ ቁመና ጤናማ እንዳልሆነ አንስተው በረቂቅ አዋጁ የቀረበው የመፍትሄ እርምጃ ተገቢ እንደሆነም ገልፀዋል።

ሆኖም በቀጣይም የመንግስት የልማት ድርጅቶች አካሄድ በተገቢው መልኩ መጤን እንዳለበትም ተናግረዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ዕዳን ወደምንዳ መቀየር አለብን በሚል በጣም ሰፊ ስራ ሲሰራ በመቆየቱ በዚህም በርካታ ድርጅቶች ትርፋማ ወደመሆን መምጣታቸውን አስረድተዋል።

የተወሰደው እርምጃም ባንኩን ጠንካራ መሰረት ላይ ለመጣል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው የገንዘብ ሚኒስቴር ዕዳውን ተረክቦ በሶስት አመት የእፎይታ ጊዜና በ10 አመት በመከፋፈል ለባንኩ ተመላሽ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።።  

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም