ቀጥታ፡

የኤርባስ ፋውንዴሽን ለጤና ሚኒስቴር የ11 ነጥብ 5 ቶን የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ የኤርባስ ፋውንዴሽን ለጤና ሚኒስቴር የ11 ነጥብ 5 ቶን የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒት ድጋፍ አድርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ድጋፉን ተረክበዋል።

የኤርባስ ፋውንዴሽንን ድጋፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነጻ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቷል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አዲስ አውሮፕላኖችን ሲያስገባ ከውጭ ሃገር የተገኙ ድጋፎችን በነጻ የጭነት አገልግሎት በመስጠት ወደ አገር እንደሚያስገባ አስታውሰዋል።

የሕክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒት ድጋፍ ላደረገው የኤርባስ ፋውንዴሽንም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን ባለቤት በመሆኑ በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ አየር መንገድ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያደርገው አመልክተዋል።

አየር መንገዱ ለጤና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ተጨማሪ አራት የኤርባስ አውሮፕላኖች በቀጣይ ወራት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡም ጠቁመዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

የኤርባስ የሽያጭ ዘርፍ ምክትል ፕሬዘዳንት ሃዲ አኩም፤ ኤርባስ ፋውንዴሽን ለጤና ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም