ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ጉባዔ መሳተፏ የስብስቡን ልምዶች በአፍሪካ ለማስፋት ተጨማሪ አቅም ይሆናል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በብሪክስ ጉባዔ መሳተፏ የስብስቡን ልምዶች በአፍሪካ ለማስፋት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ ገለጸ።

ኤምባሲው በሩሲያ ካዛን ከተማ የተካሄደውን 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ የብሪክስ አባል አገራት የኢትዮጵያ፣ ብራዚል፣ ኢራን፣ ግብጽና ህንድ ተወካዮች በተገኙበት መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ጉባዔው ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ሚና እንዲሁም ጥምረቱን የሚያጠናክር እንደሆነ አንስተዋል።

አገሪቱ በአፍሪካ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ በምጣኔ ሃብት፣በፖለቲካ ፤ዲፕሎማሲና ሌሎች መስኮች ትልቅ ሚና ያላት እንደሆነች ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት፣የተባበሩት መንግስታት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን አውስተዋል።

ይህም የብሪክስን አስተሳሰቦችና ልምዶች በአፍሪካ በማስፋት ትብብርን በማጠናከር ለማዕቀፉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ በትብብር ተጠቃሚ የሚያደርጋትን የባህል፣የሰው ኃይልና ምጣኔ ሃብት አቅም እየፈጠረች መሆኗን አንስተዋል።


 

የብሪክስ አባል አገራት በተፈጥሮ ሃብትና በቴክኖሎጂ ያላቸው አቅም እንዲሁም በተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የነቃ ተሳትፎ አላቸው ብለዋል።

ሀገራቱ በፖለቲካና ጸጥታ፣ኢኮኖሚና ፋይናንስ እንዲሁም ባህልና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ ትኩረት ያደረገ የባለብዙ ወገን ስትራቴጂክ አጋርነት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሩሲያ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከአባል አገራት ጋር ትብብርን በማጠናከር በብሪክስ ማዕቀፍ ያሉ እድሎችን ለመጠቀም እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የአባል አገራቱ መሪዎች የተሳተፉበት 16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ በሩሲያ ካዛን ከተማ ለሶስት ቀናት መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም