የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያሥላሴ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌደራል ንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ የፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ተወካዮች፣ ዳኞች፣የሲቪልማህበረሰብ ድርጅቶች፣የጠበቆች ማህበር ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በውይይት መድረኩም የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያሥላሴ የንብረት ማስመለስ አዋጁን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ንብረት ማስመለስ አዋጅ በሕገ ወጥ መንገድ የተወሰዱ ኃብቶችን ለማስመለስና የኢኮኖሚ ወንጀልን መከላከል ያለመ ነው ብለዋል።
አዋጁ ሙስናና ሌብነትን ለመከላከል የተጀመሩ አገራዊ ጥረቶችን የሚደግፍ መሆኑን ጠቁመው ወጥ የሆነ ኃብት የማስመለስ አሰራር መዘርጋትም የአዋጁ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።
አዋጁ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከግምት ያስገባ መሆኑን ገልጸው፤ የፍትሐብሔር ተጠያቂነት የሚመሰርት መሆኑን አመልክተዋል።
ከሌሎች አገራት ጋር ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችን ማድረግ ሌላው በአዋጁ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል መሆኑንም አንስተዋል።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን ማስመለስ ምርመራው የሚጀምረው ምክንያታዊ የወንጀል ጥርጣሬ ሲኖር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ተጠርጣሪው የሰነድ ማስረጃ በማቅረብ ራሱን መከላከል እንደሚችልም አንስተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተወከሉት አቶ አደነ መለስ ፤ በንብረት ማስመለስ አዋጁ የሚመለሱ ሃብቶችን ማስተዳደር የሚችል ራሱን የቻለ ተቋማዊ አሰራር መመስረት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ይህም አፈጻጸሙን ውጤታማ እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው በረቂቅ አዋጁ የሚመለሱ ንብረቶችን ማስተዳደር የሚያስችል ድንጋጌ ቢካተት የፀረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡
ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ዋለልኝ አምባነህ በሰጡት አስተያየት ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ጋር በተያያዘ ጥቆማ የሚሰጡ ዜጎች ጥበቃ ጉዳይም በአዋጁ በግልጽ ሊቀመጥ አንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስትር ደኤታ በላይሁን ይርጋ በሰጡት ማብራሪያ ምንጩ ያልታወቀ ኃብት ከተመለሰ በኋላ የሚተዳደርበት የራሱ ስርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግሥቱ ፤ውይይቱ አዋጁን በተሻለ መልኩ ለማውጣት ግበዓት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ለረቂቅ አዋጁ ግበዓት የሚሆኑ የማሻሻያ ኃሳቦች መካተታቸውን በሚመለከት ቅርብ ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።