ቀጥታ፡

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ።

በአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ (Khelfa Msabah) የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፤ የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ሲገባ በብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል እንደተደረገለት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የልዑካን ቡድን አባላቱ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ረጅም ግዜ በዘለቀው የትብብር ስራዎች በወቅታዊው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት የተወያየ ሲሆን፤ ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መስማማታቸውን ከተቋሙ የተላከ መረጃ ያመለክታል፡፡

ውይይቱን የመሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠማትን የፀጥታ ተግዳሮቶች በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑና የቀጠናውን መረጋጋት ለማረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ፤ በተጨማሪም በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሸነትን ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ ማብራራታቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡

የአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋሀ ሚስባሃ በበኩላቸው ተቋማቸው ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር የጀመራቸውን የመረጃ ልውውጥ ስራዎችንና የቴክኒካዊ መረጃ የትብብር ማዕቀፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የልዑካን ቡድን አባላቱ ከውይይቱ በኋላ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሄር እና ከሌሎች የተቋሙ አመራሮች ጋር በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የጎበኙ ሲሆን፤በጉብኝቱ ወቅትም የአልጀሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት አቅም ማድነቃቸውንና ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፤ ለጎረቤቶቿም ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በማቅረብ ግልጋሎት የሚሰጥ የትብብር እና አብሮ የመልማት ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ መግለፃቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለልዑካን ቡድኑ ያብራሩ ሲሆን፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም አንዱና ግንባር ቀደሙ መገላጫ መሆኑን እና ከሀገሪቱ አልፎ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲሁም ለቀጠናው የሚያበረክተው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም