ቀጥታ፡

የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ መገንባት መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው

ሰቆጣ ፤ ጥቅምት 26/2017 (ኢዜአ)፡-  የሰቆጣ -ፅፅቃ -መሸሃ አካባቢዎችን የሚያስተሳስረው የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ መገንባት መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያለውን  ቁርጠኛ አቋም ማሳያ መሆኑ ተገለጸ።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር  የስራ ሃላፊዎች በ350 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ከነሐሴ 2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ ጎብኝተዋል። 

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ በጉብኝቱ ወቅት፤ የተከዜ ወንዝ ድልድይ መገንባት የሰሃላና የዝቋላ ወረዳዎች ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጡን ተመልክተናል ብለዋል።  

ይህም በህዝቡ ዘንድ የልማት ጥያቄ ሆኖ የቆየውን ልማት መልስ ማግኘቱ  ክረምት እስከ በጋ ያለምንም ችግር የግብርና ምርትና የኢንዱስትሪ ውጤቶች እንዲጓጓዙ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በተለይም የሰሃላ ወረዳ ነዋሪዎች ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የአንቡላንስ፣ የህዝብ ትራንስፖርትና ሌሎች የጭነት አገልግሎቶች ማስቀጠል መቻሉን አስረድተዋል።  

በአሁኑ ወቅት ድልድዩ እስከ 20 ቶን ክብደት ያላቸውን ተሽከርካሪዎችን ብቻ የሚያሳልፍ ሲሆን ፤ አገልግሎቱን ወደ 40 ቶን ለማሳደግ የሚያስችል ስራ በቀጣይ ይሰራል ብለዋል። 

የድልድዩን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘምም ህብረተሰቡም ሆነ አሽከርካሪዎች የድልድዩ የመሸከም አቅም እስኪሻሻል በድልድዩ ላይ የተጣለውን የክብደት ገደብ ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል። 


 

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ሽታው አዳነ በበኩላቸው፤  የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ መገንባት የሰሃላና ዝቋላ  ወረዳ ህዝብ የነበረበትን ችግር ያቃለለ መሆኑን ገልጸዋል። 

የክልሉ መንግስት ለድልድዩ ግንባታ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃቱ የሚመሰገን ነው ያሉት አቶ ሽታው ፤ በቀጣይም የድልድዩን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። 

የሰቆጣ-ፅፅቃ-መሸሃ የሚያስተሳስረው የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ 146 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤  ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደርን ከሰሜን ወሎ ዞን ጭምር ለማስተሳሰር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም