መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 26/2017 (ኢዜአ)፦ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጠቅላላ ጉባኤና የልምድ ልውውጥ መድረክ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት መሰረተ ልማትን የማስፋፋትና ከተሞቹን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ በትኩረት መከናወን አለበት፡፡
በዚህም በከተሞች የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሰራዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የከተማ መሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡።
በከተሞች የዘመነ አገልግሎት መስጠትና በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያለውን ህዝብ ታሳቢ ያደረገ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት ማከናወን ይገባልም ብለዋል፡፡፡
በፕላን የሚመሩ ከተሞችን በመፍጠር ህገወጥነትን መከላከልና ስራዎችን በቴክኖሎጂ በማገዝ የመሬት ሀብትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸው ይህም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ከግል ባለሃብቱ ጋር መቀናጀት እንዲሁም የከተሞችን የገቢ አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
በ2013 ዓ.ም 10 ቢሊየን የነበረው የከተሞች ገቢ አሁን 47 ቢሊየን መድረሱን ገልጸው በ2017 የገቢ አቅሙን ወደ 60 ቢሊየን ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ቦርድ ፕሬዝዳንትና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው የትብብር መድረኩ ለነዋሪዎች ምቹ ከተሞችን ለመፍጠር ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በትብብር መድረኩ 101 ከተሞች አባል መሆናቸውን ገልጸው የከተማ ከንቲባዎችና አመራሮች እርስ በእርስ ልምድ በመለዋወጥ የተመጣጠነ የከተማ እድገት እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሆነችውን ሀዋሳ በፕላን የተከተመች መሆኗ እንደ ምቹ እድል አንስተው የኮሪደር ልማትና የ'ስማርት ሲቲ' ግንባታ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የሃዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራም የመስክ ጉብኝት ተደርጓል፡፡