በዞኑ የሰፈነው ሰላም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናከሮ መቀጠሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሰፈነው ሰላም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናከሮ መቀጠሉ ተገለጸ
ደብረብርሃን፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሰፈነው ሰላም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
"ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ የመንግስት ሰራተኞች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ እንደገለጹት፤ የሰላም አማራጭ ጥሪን ባለመቀበል በጥፋት መንገድ ለመቀጠል እየሞከረ ያለው የጥፋት ቡድን በህብረተሰቡ ድጋፍና በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እየተመታ ነው።
በዞኑ የሰፈነው ሰላም በህብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ የመንግስት ሰራተኞች ሙሉ ጊዜያቸውን ህዝብና መንግስትን በታማኝነት በማገልገል በጥፋት ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ከመደገፍ ባሻገር ተላላኪዎችን ማጋለጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መንግስት ትናንትም ዛሬም ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ተናግረዋል።
ሆኖም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተው የጥፋት መንገድ የተከተለው ቡድን እንደማይሳካለት ገልጸዋል።
በመንግስት የተጀመረው ህግ የማስከበር ተግባር ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አመልክተው፤ የመንግስት ሰራተኞች የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎችን አጋልጠው ለህግ እንዲሰጡ አሳስበዋል።
የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር የህዝብ ተሳትፎና የፖለቲካ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ ውይይቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በእውነታ ላይ ተመስርቶ የህዝብ ተሳትፎን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት ሰራተኞችም በስራ ገበታቸው ላይ በመገኘት ከአድሏዊ አሰራርና ከሙስና በፀዳ መንገድ ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ፀሐይ ግርማ በሰጡት አስተያየት፤ የነበረው ችግር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው፤ ችግሩን በንግግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላትና የመንግስት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።