የአክሱም ሐውልት ና የነገስታት መቃብር ሥፍራን የማጥናት ተግባር እንደሚከናወን ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአክሱም ሐውልት ና የነገስታት መቃብር ሥፍራን የማጥናት ተግባር እንደሚከናወን ተገለጸ
አክሱም፤ ጥቅምት 26/2017 (ኢዜአ)፦ የአክሱም ሐውልት ና የነገስታት መቃብር ሥፍራን ለማጥናት ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡ ተገለጸ።
የአክሱም ሐውልት ቁጥር ሶስት እና በስሩ የሚገኙ የነገስታት መቃብር ሥፍራዎች ለማጥናት የማስጀመርያ የፕሮጀክት ሳይት ርክክብ ዛሬ ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ለሥራው ማስፈጸሚያ የሚውል 115 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። ስራውም በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት ይከናወናል።
በጎርፍና በሌሎች ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸው ጥንታዊ የነገስታት መቃብር ለማደስና ለቱሪስት በሚመች መልኩ ለማስተካከል ሥራው እንደሚከናወን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም የዘመመውን የአክሱም ሐውልት ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የማቃናት ሥራ በጣሊያኑ ''ላታንዚ'' ኩባንያ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የአክሱም ሐውልትና የነገስታት የመቃብር ሥፍራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ባህልና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ መሆናቸውን አውስተዋል።
በኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን የሙዚየም ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ "የዘመመውን የአክሱም ሐውልት ቁጥር ሶስት ሳይት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎበት የማቃናት ሥራው ይከናወናል" ብለዋል።
የነገስታት መቃብር ሥፍራው ዘመናትን ያስቆጠረ በመሆኑ ተሰነጣጥቆ አደጋ ላይ መሆኑንን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሥራው በተመሣሣይ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አፅባሃ ገ/እግዛብሄር (ዶ/ር)፤ የአክሱም ህዝብ የሐውልቱን የመጠገንና የነገስታት መቃብር ሥፍራዎች የመጠናት ሥራን በጉጉት ይጠብቀው እንደነበረ አውስተዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለሥራው ስኬታማነት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።