ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቅርሶችን በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገችው ያለው ጥረት ለውጥ አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቅርሶችን በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገችው ያለው ጥረት ፈጣን ለውጥ ማምጣቱን የአለም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለፁ።

የሰላም ሚኒስቴር በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ከመሐመድ ቢንዛይድ ፎር ሁማኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው የአለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተጠናቋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድነት ፓርክ የተለያዩ መዝናኛዎችን ፣እፅዋቶችና ታሪካዊ ቅርሶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ከተሞች እየታዩ ያሉ ለውጦች የሚደነቁና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መልካም ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን የሃይማኖት ጉባኤ ተወካይ ፔርተር ያይድንግ ኢትዮጵያ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ሀብት እንዳላት በመጥቀስ ታሪካዊ ቅርሶቹ ይዘታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፉ ትልቅ ስራ መስራቷን በበጎነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛችና ለሌሎች የነፃነት ትግል ተምሳሌት የሆነች ታላቅ አፍሪካዊት አገር እንደሆነችም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጎረቤት መሆናቸውን በመጥቀስ፥ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

ከደቡብ አፍሪካ የሃይማኖቶች ምክር ቤት የመጡት ራቢ ግላድ ፍሪድማን አንድነት ፓርክን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

የአንድነት ፓርክ የኢትዮጵያ ታሪክ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ መሰራቱን በመጥቀስ ለሌሎች ሀገራት ልምድና ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩ የሀገሪቱን ታሪክ በሚገባው መልኩ በማስቀመጥ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርግ ከመሆኑ በላይ ያማረ፤ብዙ ትምህርትና ልምድ የሚሰጥ ቦታ ነው ብለዋል፡፡


 

በኡጋንዳ የሙስሊም ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ ሙሀመድ አሊ አሉማ ኢትዮጵያ ቅርሶችን ጠብቆና አልምቶ በመያዝ ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

የአዲስ አበባ የልማት እድገት መዲናዋ ከአፍሪካና አለም አቀፍ ትላልቅ ከተሞች ጋር እንድትወዳደር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሰል የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም