ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና ለወ/ሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት መጻሕፍት አበረከተ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና ለወ/ሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት መጻሕፍት አበርክቷል።

ኢዜአ ለትምህርት ቤቶቹ ዛሬ ያበረከታቸው መጻሕፍት የታሪክና የሳይንስ፣የስነ-ጥበብ፣ ልብወለዶች እና ሌሎች ይዘቶችን የያዙ ናችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የህዝብ ግንኙነትና የስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ወንድይራድ መጻሕፍቶቹን ለተቋማቱ አስረክበዋል፤

 አቶ ዮሀንስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  ኢዜአ ዜናና ዜና ነክ ጉዳዮችን በተለያዩ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽ አግባቦች መረጃዎችን  ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባለፍ በማህበረሰብ አገልግሎት ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ።


 

በዛሬው እለትም የትምህርት ተቋማትን አቅም ለመገንባት ታሳቢ በማድረግ ከ1000 በላይ መጽሀፍትን ለእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና ለወ/ሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ማበርከቱን አንስተዋል።

ለትምህርት ቤቶቹ የተበረከቱት መጻሕፍት ተቋሙ በተለያዩ ጊዜ ካከማቻቸው መካከል  እንደሆኑም ተናግረዋል። 

መጻሕፍቱ ትውልድን ለመገንባት የሚጠቅሙና በርካታ ይዘት ያላቸው በመሆናችው ለትምህርት ቤቶቹ የሚሰጡት ፋይዳ ከፍተኛ ነው ሲሉ ጠቁመዋል ።

የወ/ሮ ቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወካይ ወ/ሮ ሰናይት ማንደፍሮ በበኩላችው ለተደረገላቸው የመጻሕፍት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው መጻሕፍቱ መምህራንና ተማሪዎች እውቀታቸውን ለማዳበር ትልቅ ጥቅም ይኖራቸዋል ብለዋል።


 

በትምህርት ቤቱ አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር ለማድረግም የተበረከተላቸው መጻሕፍት የራሱ አበርክቶ አንደሚኖረው አንስተዋል።

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቤተመጻሕፍት አስተባባሪና አሰልጣኝ ተመስገን ክብረኩሉ ኢዜአ ላደረገላው የመጻሀፍት አበርክቶ አመስግነው መጻሕፍቶቹ የአሰልጣኞችን እና የተማሪዎችን እውቀትና ክህሎት ለማዳበር አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም