ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የማህበረሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የማህበረሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አጠናቀቀ
ቦንጋ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ሲያካሄድ የቆየውን የማህበረሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ አጠናቀቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በሰጡት በመግለጫ ባለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ የማሰባሰብ እና የተወካዮች መረጣ ሂደት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ሙሉጌታ፣ ተሳታፊዎቹ ያለምንም ተፅእኖና ጣልቃ ገብነት ወክለው የመጡትን ማህበረሰብ ሀሳብ ማንሳታቸውን ተናግረው በሀገራዊ ውይይት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችም መመረጣቸውን አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ ተሞክሮዎችን በመጠቀም የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች መረጣው በተሳካ መልኩ መካሄዱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ቀናት ከክልሉ ከተወከሉ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ከተቋማት፣ከፖለቲካ ፖርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
ለተሳታፊዎች አጀንዳን በተመለከተ ቀደም ብሎ ግንዛቤ መፈጠሩን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።