ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማሳለጥ ዕድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማሳለጥ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆየው በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና 19ኛው የከፍተኛ ንግድ ባለሙያዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡  

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአህጉሪቱ የተቀናጀ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር የሚችል ነው፡፡


 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ ሀገራት ከድህነት ለመውጣት በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት በትኩረት የሚሰራበት የኢኮኖሚ አንድነት መፍጠሪያ መደላድል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያም እንደ አንድ አባል ሀገር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗን አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የንግድ ቀጣናው የጎላ አበርክቶ እንዳለው እንረዳለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በፓን አፍሪካ እሳቤ መሰረት አህጉራዊ የኢኮኖሚ ዑደት መፍጠር እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማሳለጥ ምቹ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡


 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሀፊ ጾጤፂ ማኮንግ ዶ/ር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከንግድ ስምምነትም በላይ የአፍሪካ አንድነት ማጠናከሪያ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የነፃ የንግድ ቀጣናውን ገቢራዊ ለማድረግ የሁሉንም አባል ሀገራት ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊ እንዲሆን ምሳሌ ሊሆን የሚችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የከፍተኛ የንግድ ኃላፊዎች ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሀሺል አብደላህ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡

እንደ አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና አይነት የትብብር ማዕቀፎችን ገቢራዊ ማድረግ ካልተቻለ በአህጉሪቱ በሚተገበሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡

ከጥቅምት 11 እስከ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የአገልግሎት ንግድ ኮሚቴ፣ የኢንቨስትመንት እና የዲጅታል ንግድ ኮሚቴ ስብሰባዎች በአዲስ አበባ መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

የነጻ ንግድ ቀጣናው የንግድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ጥቅምት 30 እና ህዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም በመዲናዋ ሊካሄድ መርሀ ግብር ወጥቶለታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም