ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድግ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን አየር መንገዱ በኢንዲስትሪው ውስጥ ያለውን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድግበት መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብቷል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የአየር መንገዱ ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ዛሬ አዲስ አበባ ሲገባ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶች አቀባበል ተደርጎለታል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ አየር መንገዱ በቴክኖሎጂና በመሠረተ ልማት እየበለጸገ ይገኛል ብለዋል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ 350-1000 አውሮፕላን ለአየር መንገዱ ቀጣይ ዕድገት ትልቅ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኤ350-1000 አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን የሚያስቀጥልበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድግበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ፤ ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ተደራሽነቱን ይበልጥ በማሳደግ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ አቅም የሚጨምርለት ነው ብለዋል።
አውሮፕላኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ መዳረሻዎቹን እያሰፋ ለሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪነቱን እንደሚያሳድግለት ነው የተናገሩት።
" Ethiopia Land of Origin " የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሮፕላኑ 400 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱ ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ አየር መንገዱ 124 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙን መናገራቸው ይታወሳል።