የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረሀብን በዘላቂነት ለማጥፋት አፋጣኝና የተቀናጀ እርምጃ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረሀብን በዘላቂነት ለማጥፋት አፋጣኝና የተቀናጀ እርምጃ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረሃብን በዘላቂነት ለማጥፋት መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታትና የተቀናጀ የተግባር እርምጃ ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ማስመዝገቧንም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ)፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና የዓለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) በጋራ ያዘጋጁት ከረሀብ ነፃ ዓለም /world without hunger/ ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የአቡዳቢ አልጋወራሽ ሼህ ኻሊድ ቢን መሃመድ ቢን ዛይድ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ገርድ ሙለርና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ እንዳሉት፥ ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም በመፍጠር ሂደት ውስጥ የአየር ጠባይ ለውጥና መዋቅራዊ ችግሮች ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ ነው።
ይህ ደግሞ ፈጠራ የታከለበት ችግር ፈቺ መፍትሄ ይሻል ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር አንጻር የምግብ ፍላጎት በእጅጉ ማደጉን ጠቅሰው፥ ይህን ፍላጎት ለመመለስም ምርታማነትን ከማሻሻል በላይ በግብርና ዘርፍ ላይ የሚታዩ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት ላይ አፋጣኝ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚታረስ መሬትን በእጥፍ በመጨመር፣ የግብዓት አቅርቦትና ዘመናዊ እርሻን በመተግበር ምርታማነትን ማሻሻል መቻሉን በመጥቀስ።
በተለይ በስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎና ገብስ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ባለፈው ዓመት ብቻ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱን አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነትም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፣ በመርሃ ግብሩም እስካሁን 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።