ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ
ሰመራ ፤ ጥቅምት 26/2017(ኢዜአ)፦ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከአፋር ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሸን ቢሮ ጋር በመተባበር በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ ነው።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ፋይናንስ አመራር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍቃደ ተክለማርያም እንዳሉት፤ ከተሞች የገቢ ምንጫቸውን ለይተው መንቀሳቀስ አለባቸው።
ከተሞች መሠረተ ልማታቸው የተሻለ እንዲሆን ለማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ በቂ ትኩረት መስጠት እንዳለባውም አንስተዋል።
ማዘጋጃ ቤቶች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች የተሻለ ገቢ መሰብሰብ እንዲችሉም የገቢ ምጣኔያቸውን በሚመለከተው አካል በአግባቡ ማስወሰን እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢያቸውን በማሣደግ ህብረተሰባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፋር ክልልም የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን በማጠናከር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ጎን ለጎን የባለቤት እና የተሳታፊነት ስሜት እንዲጎለብት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የአፋር ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊም፣ በክልል ደረጃ የተሻለ ገቢ በመሠብሰብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ ከተሞች ማዘጋጃቤታዊ ገቢ የመሠብሰብ አቅማቸውን ማሳደግ ላይ ተከታታይነት ያለው እገዛና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አወል አብዱ በበኩላቸው በሚኒስቴሩ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ገቢ የመሰብብ አቅምን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በተለይም በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታትና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ለማዘመን የሚያግዝ እንደሆነ አክለዋል።
ስልጠናውን እየወሰዱ ካሉት ውስጥ የአዋሽ ሰባት ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ ኢብራሂም፣ በስልጠናው የቀሰምነውን የገቢ ማስገኛ አማራጮችን በመጠቀም ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።
ስልጠናው እስካሁን የሚሰራውን የዘመቻ አሰራር በማስቀረት ለገቢ ትኩረት በመስጠት ወጥነት ባለው መልኩ ስራዎች እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።